Wednesday, 2018-12-12, 0:21 AM
ETHIOPIAN POLITICS current event and news
Main Registration Login
Welcome, Guest · RSS
Site menu
  news
  news
  curency
  Calendar
  «  September 2011  »
  SuMoTuWeThFrSa
      123
  45678910
  11121314151617
  18192021222324
  252627282930
  Site friends
   
  Main » 2011 » September » 26 » አዉራምባ - “ሕዝቡን እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ ነፃ ሊያወጣው አይችልም”-ዶር ነጋሶ September 26th, 2011
  11:30 PM
  አዉራምባ - “ሕዝቡን እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ ነፃ ሊያወጣው አይችልም”-ዶር ነጋሶ September 26th, 2011

  ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሰሞኑን መንግሥት በአሸባሪነት የጠረጠራቸውን ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ማሰሩ ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ እና በሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ ሱራፍኤል ግርማ ከቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና ከወቅቱ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ሊቀ-መንበር ከሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

  የሰሞኑን የእስር ሂደቶች ፓርቲው እንዴት ነው የሚመለከተው?

  በተለያዩ ጊዜያት እንደገለፅነው፣ ፓርቲያችን ለፍትህና ለዴሞክራሲ ይታገላል፤ ሕገመንግስቱ ያጎናፀፈንን መብቶች በመጠቀም መታገላችንን እንቀጥላለን። ትግላችንም ሰላማዊ መሆን እንዳለበት እናምናለን። በእኛ አመለካከት የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚና የብሔራዊ ም/ቤቱ አባላት፣ እንዲሁም የሌሎች ታጋዮች መታሰር የሚያመለክተው ጠንካራ ተቃዋሚዎችን የማጥፋት መንገድ መያዙን ነው። የእኛን ድርጅትንም ሆነ ሌሎች ለሰላምና ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ድርጅቶችን የማዳከሚያ ሥልት ነው።

  የታሰሩትን ሰዎች ስናያቸው ወጣቶች ናቸው። በጣም ጠንካራ ታጋዮች ናቸው። እነሱን በማሰር ድርጅቱን የሚያዳክሙ ሊመስላቸው ይችላል።

  "እስሩ ወደ እኛም ሊመጣ ይችላል” የሚል ሥጋት በሌሎች አመራሮች ላይ አለ እንዴ?
  ለምን እንፈራለን? የምንፈራበት ምክንያት የለም። እኛ በግልፅ እንደምንናገረው ሰላማዊ ታጋዮች ነን። ሰላማዊ ትግላችንን መንግስት አጣሞ በመተርጎም ሊያስረን ይችላል። ግን ይሄ አያስፈራንም። ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ለመብቱ እንዲታገል የማያቋርጥ ጥሪ እናደርጋለን። ይሄንን ለሽብር እንደማነሳሳት ከቆጠሩት ምንም ማድረግ አይቻልም።

  ገና ለገና ያስሩናል ብለን ከትግላችን አንስተጓጎልም። የታሰሩት ሰዎች የምር አሸባሪ ላለመሆናቸው ምንድን ነው ማረጋገጫችሁ?

  ልጆቹን [የታሰሩትን] እናውቃቸዋለን እኮ። እሁን ለምሳሌ አንዷለም እንኳንስና አሸባሪ ሊሆን ይቅርና ከሰላማዊ ትግል ውጪ የሚያስቡ ወገኖችን በጣም ነው የሚኮንነው። ነፍጥ አንስቶ የመሳሪያ ቃታ ለመሳብ ይቅርና ከሰዎች ጋር በፍቅር ስለመኖር የሚሰብክ ትሁት ልጅ ነው።

  እነ ናትናኤልም ቢሆኑም በአንድነት ሰላማዊ አካሄድ ከልብ አምነው የሚንቀሳቀሱ ልጆች ናቸው። ለዚህ
  ነው ንፅህናቸውን የምንመሰክረው።

  እርስዎ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ነበሩ። ኢህአዴግን በደንብ እንደሚያውቅ ሰው እነዚህን እርምጃዎች እንዴት ያዩዋቸዋል?

  ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ተናግሬዋለሁ … የኢህአዴግ አስተሳሰብ የተቃኘው በነማኦ እና በነስታሊን መንገድ ነው። ስለዚህ ተቀናቃኞቹን ሁሉ በማጥፋት ነው የሚያምነው። በምንም ጉዳይ ላይ ከእሱ ውጪ ትክክለኛ ሐሳብ ያለው አካል ያለ አይመስለውም። "እኔ ይቺን አገር ካልመራሁ ትበታተናለች” የሚል እኮ ነው።

  እራሱን በዚህ መልኩ ተመልክቶ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ ነበር ግን ሌሎቹን ተቃዋሚዎቹን ደግሞ በፀረ-ሰላምነት፣ በሽብርተኛነት በመፈረጅ እንዲጠፉ ያደርጋል።

  ከምንም በላይ ደግሞ በ1993 ዓ.ም ግንባሩ በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ "አገሪቷን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የግድ ቀጣዩቹን 20 እና 30 ዓመታት በገዢነት መቀጠል አለብኝ” ብሏል። ስለዚህ ይህንን "ዕቅዱን” ሊያጨናግፉ የሚችሉ ወገኖችን ለመከላከል ከቀየሳቸው ዘዴዎች ውስጥ አንዱ የሰሞኑ ዓይነት ዘመቻዎች እና ቀፍዳጅ ሕጎች ዋንኞቹ ናቸው።

  የአባሎቻችሁ መታሰር በፓርቲያችሁ ላይ ያመጣው ተፅዕኖ ምንድን ነው? እርግጥ ነው በአባሎቻችን መታሰር አዝነናል። ነገር ግን የእስሩ ምክንያት ስለሚገባን ራሳችንን አጠናክረን በመቀጠሉ ላይ ነው ያተኮርነው። ከምንም በላይ ደግሞ ድርጅታችን በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ የተደገፈ ስላልሆነ የታሰሩት አባሎቻችን ይሰሩት የነበረውን ሥራ ሌሎች አባሎች እንዲሸፍኑት አድርገናል። በሌላ በኩል ግን ምንም እንኳን እስሩ የታቀደው እኛን ለማሸማቀቅና ለማዳከም ቢሆንም እኛ የሚደርስብንን ጫና ይበልጥ ለመቋቋም የሚያነቃቃ እና የሚያጠናክር አድርገን ወስደነዋል።

  በአንድ በኩል የሚያጠናክራችሁ እንደሆነ እየለፃችሁ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አባሎቻችሁ እየታሰሩ ነው … ይሄ በሰላማዊ ትግል ተስፋ አያስቆርጥም?

  ይሄ እርምጃ በሰላማዊ ትግል ተስፋ ሊያስቆርጥ አይገባም። እንዲያውም አባሎቻችን በቆራጥ ሰላማዊ ታጋይነታቸው መታሰራቸው ለሌሎች አርዓያ በመሆን የሚያበረታታ ነው።

  በቅርቡ ፓርላማው በአሸባሪነት አምስት ድርጅቶችን ሰይሟል፤ ይሄ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያስከተለው …አዎ፤ ውሳኔው አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደገውን ጥረት ያጨናገፈና በር የዘጋ ነው። የትጥቅ ትግልን እንደአማራጭ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ወገኖችን ወደ ሰላማዊ ጎዳና ለመመለስ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ መፈረጁ ተገቢ አይደለም።

  በመሰረቱ እኮ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ከሰፈነ የትጥቅ ትግልን እንደአማራጭ የሚያራምዱ አይኖሩም። ስለዚህ መንግሥት ሰላማዊ ታጋዮችን ማሰሩ በሰላማዊ ትግል ተስፋ ለቆረጡ ወገኖች ጥሩ ማሳመኛና መከራከሪያ ከመሆኑ ውጪ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ አይሆንም።

  የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ሲፀድቅ በፅኑ ተቃውማችሁ ነበር። የዛኔ የፈራችኋቸው ነገሮች አሁን እየተስተዋሉ ናቸው? በትክክል። አዋጁ በብዙ መንገድ በሕገመንግስቱ የተደነገጉትን ሰብዓዊ መብቶች እንደሚጥስ በማስገንዘብ ነበር የተቃወምነው። ለምሳሌ፤ በግል እኔ ላይ ቁርሾ ያለው ሰው ‹‹ሽብርተኛነው›› ብሎ በመጠቆሙ ብቻ ልታሰር እችላለሁ። መንግስት በፈለገው መንገድ አጣርቶ አንድን ሰው በሽብርተኛነት ለመፈረጅ መረጃና ማስረጃ ሳይኖረው ሲቀር የተከሰሰው ሰው ነው ማስረጃ በማቅረብ ራሱን ነፃ ማውጣት ያለበት።

  ይሄ እንግዲህ የመንግስትን ኃላፊነት ወደ ግለሰቡ ማላከክ ነው። ሌላው የጠረጠሩትን ሰው እስር ቤት ሲያስገቡ በተፋጠነ ፍርድ ውሳኔ እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ ለረዥም ቀናት (እስከ አራት ወር) እስር ቤት አቆይተው ምርመራ ያካሂዳሉ። መጀመሪያ ካሰሩ በኋላ ነው መረጃና ማስረጃ የሚያሰባስቡት። ከዚህ በተጨማሪ የሕገ ወንግስቱን አንቀጽ 19 በመጣስ ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው እንዳይገናኙ ይከለክላሉ።

  ውጪ አገራት ከሚገኙና በአሁኑ ሰዓት በአሸባሪነት ከተሰየሙ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች ጋር እርስዎም ሆኑ ሌሎች የፓርቲዎ ሰዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ወዳጅነት ነበራችሁ። አሁን ባለው ሁኔታ ከእነዛ ፖለቲከኞች ጋር ከፖለቲካ ሥራ ውጪ ባሉ የግል ጉዳዮች ላይ እንዳትነጋገሩ አዋጁ ይከለክላል?

  የግለሰብን ነፃነት ከመዳፈር አንፃር . . .እንበልና ከዶ/ር ብርኃኑ ነጋ ጋር ዘመድ ብንሆንና ስለጤንነታችን፣ ስለቤተሰብ መረጃ ከተለዋወጥኩኝ "ከሽብርተኛ ጋር መረጃ ተለዋውጧል” ብለው ያስሩኛል። አሁን እንግዲህ የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆነው አቶ ሌንጮ ለታ የስጋ ዘመዴ ነው። የልብ ጓኛዬም ነበር። እና አሁን ለእሱ በኢ-ሜይል ሰላምታ ብልክለት እንኳን ከማሰር ወደኋላ አይሉም። ይሄ እንግዲህ ሰብዓዊ መብትን በግልፅ የሚጥስ ነው። አዋጁ መግቢያ ላይ፤ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ እንዲወጣያስፈለገው በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች ሽብርተኛነትን በቢቂ ሁኔታ መከላከል ስላላስቻሉ መሆኑ ተገልጿል። እውን በሥራ ያሉት ሕጎች ሽብርተኛነትን ለመከላከል ብቁ አልነበሩም?

  በመሠረቱ ከሆነ በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች በጣም ጥብቅ (ቀፍዳጅ) ከመሆናቸው አንፃር ሽብርተኛነትን መከላከል አያቅታቸውም ነበር። ዋናው ነገር ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹን ይፈራል። የተቃውሞ ትግልን ለማዳከምና ዜጎችን ለማስደንገጥ ሲል የፈጠረው ነገር ነው።

  አድነት ፓርቲ ከዚህ በኋላ ንፅህናቸውን የሚመሰክርላቸው አባላቱንም ሆነ ሌሎች "የፖለቲካ እስረኞችን” ለማስፈታት ምን እያረገ ነው? እንዲሁም በየክልሉ ላሉ አባሎቹ ምን ከለላ ነው የሚያደርገው?

  እኛ ለአባሎቻችን ምንም ዓይነት ዋስትና መስጠት አንችልም። በፕሮግራማችን አምነውና ሕገ-ደንቡን ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ አባሎቻችን ዋና ዓላማቸው ትግሉን ማጠናከር እንጂ ስለራሳቸው መጨነቅ አይደለም። ፓርቲያችንን የሚቀላቀሉ ሰዎች እንዲያውቁት የምናደርገው በመጀመሪያ ደረጃ ትግል ውስጥ ሲገቡ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ሊከፍሉ እንደሚችሉ ማስገንዘብ ነው። ይኼንን አውቀው ነው እኛ ጋር የሚገቡት እንጂ ከለላ ፍለጋ አይደለም። ከለላ ፈልጎ የሚመጣማ ቀድሞውኑ ታጋይ አይደለም ማለት ነው።

  ይኸ ሲባል ግን ታጋይ አባሎቻችንን ለአደጋ አጋልጠን ዝም ብለን አንጥላቸውም። በተቻለን መጠን የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ፣ ወከባና እንግልት የሚደረስባቸውን ለመታደግ እንንቀሳቀሳለን። አሁን ሰሞኑን የታሰሩብንን አባሎች ለማስፈታት ግብረ-ኃይል አቋቁመናል። ግብረ-ኃይሉ በሕጋዊ፣ በሰብዓዊ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች፣ በሕዝብ ግንኙነት እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ነው።

  "ዓላማችን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ነው” ትላላችሁ። ግን አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ይኸን እንዴት ነው የምታሳኩት?

  ያሉትን ወቅታዊ ችግሮች በጋዜጣዊ መግለጫዎችና በሌሎች መንገዶች እየለፅን ነው። ኹኔታዎቹን ስንገልፅ ሕዝቡ ደግሞ ከችግሩ ለመውጣት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለበት። ሕዝቡ ራሱ ለመብቱ፣ ለነፃነቱና ለዴሞክራሲ ካልታገለ የእኛ ሥራ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ሕዝቡን እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ ነፃ ሊያወጣው አይችልም። ሕዝቡ የተነፈገውን መብቱን ለማስከበር ራሱ መታገል አለበት።

  እኛም ይኼን ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወንን ነው። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናት ያደጉ ባለሙያዎችን እየጋበዝን ውይይት እያደረግን ነው። ቀስ ብለን ደግሞ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሔድ አቅደናል። የአባላት ምልመላና የፓርቲ ማደራጀት ሥራም በከፍተኛ ሁኔታ እያከናወንን ነው።

  ከዚሁ ጋር ተያይዞ መግለጫዎችን ከመስጠት ባለፈ ሌሎች ሰላማዊ የተቃውሞ ሥልቶችን አትጠቀሙም። ምንድን ነው ምክንያቱ?

  ሌሎቹን ሥልቶች መጠቀም ግድ የሚለን ደረጃ ላይ አልደረስንም ብለን ስለምናስብ ነው። ምክንያቱም ከምርጫ 97 በኋላ የሆነውን ነገር ማንም ኢትዮጵያዊ ያስታውሳል። ከዛ እንደገና መሪያችን ብርቱካን ሚደቅሳ ታሰረች። እንዲሁም የውስጥ ችግሮች ነበሩብን። እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት እየሞከርን የምርጫው ጊዜ ደረሰ። በአንድ በኩል ከኢህአዴግ የሚመጡብንን ችግሮች ስንከላከል፣ በሌላ በኩል እነዚህን የውስጥ ችግሮች ለመፍታት ስንንቀሳቀስ ነው የቆየነው።

  ከዚህ በኋላ ነው ሁሌ ኢህአዴግ ላይ ለድክመቶቻችን መንስኤ ጣት ከመቀሰር ወደ ራሳችን መመልከት የጀመርነው። ከዚህ አንፃር የመጀመሪያ ግምገማ አካሂደን በግምገማው ውጤት መሰረት የሥራ አስፈፃሚውን አባላት አቀያይረናል። 18 የነበረውን የሥራ አስፈፃሚ አባላት ቁጥር ወደ 13 እንዲቀነስና ወጣቶች ወደ አመራር እንዲመጡ ተደርጓል።

  ሌሎች ሰላማዊ የትግል አካላት "መቼ ነው መንግስትና ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን አጥብበው ወደ ውይይት የሚመጡት?” የሚል ጥያቄ እያነሱ ነው። የእናንተ ፓርቲ በዚህ ረገድ ምን እየሰራ ነው?

  በአንድነትም ሆነ በመድረክ በኩል ከሁለት ዓመት በላይ ነው "ወደ ውይይት እንምጣ” የሚል ጥሪ ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለመንግስት ስናቀርብ የቆየነው። እኛ ነገሮች እንዲካረሩ አንፈልግም። በዚያው ልክ ደግሞ ነገሮች እንዳይካረሩ በመስጋት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጣሱ እያየን ዝም አንልም።

  ከመብት ጥሰቶች ባሻገር አስከፊ የሆነ ድህነት ሕዝቡን እያሰቃየ ነው፤ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት በየቀኑ እየጨመረ ነው። እነዚህ ችግሮች ደግሞ ጊዜ ሳይሰጣቸው ሊፈቱ የሚገባቸው ናቸው። ለችግሮቹም መፍትሔ ለመፈለግ ኢህአዴግ ‹‹ለሁሉም መፍትሔው እኔ ጋር ብቻ ነው ያለው›› የሚለውን ነገር መተው አለበት። እኛ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ጥሪ እያቀረብን ነው። ግን ሊሰማን ፍቃደኛ አልሆነም።

  ሥልቶችን ለምሳሌ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ፣ የረሐብ አድማ፣ ቤት ውስጥ መቀመጥ ወዘተ ወደ ማድረጉ የምንመጣው ያሉብንን የቤት ሥራዎች ከጨረስን በኋላ ነው። አሁን ለምሳሌ ሰላማዊ ሰልፍ ዝም ተብሎ አይወጣም - አደገኛ አካሄድን የሚከተል ገዢ ፓርቲ ባለበት አገር ሰልፍ ቢጠራ የሚሆነውን ነገር ማሰብ ይከብዳል። ሰርጎ ገቦቹን በማስገባት ሆን ብሎ ሰላማዊውን ሰልፍ ሊያውክና አቅጣጫውን ሊያስቀይስ ይችላል። ስለዚህ ይህንን አስቀድሞ ለመከላከል ብዙ ቅድመ ዝግጅቶችን ይጠይቃል።

  ሌሎች ፓርቲዎችም በጋራ ሰልፍ እንድንጠራ ጥያቄ አቅርበውልን ነበር። ግን እንዳልኩህ ጉዳዩ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅና በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ስለሆነ ጥያቄያቸውን ለጊዜው አልተቀበልነውም።

  በተጠቀሱት ምክንያቶች አስገዳጅነት ነው እንጂ ከኑሮ ውድነቱ፣ ከሥራ አጥነቱና ከፖለቲካዊ ቀውሶቹ አኳያ በአሁኑ ሰዓት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራት ይቻል ነበር።

  ከሰላማዊ ትግል ውጪ ያለውን የፖለቲካ አካሄድ የምትኮንኑት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካላችሁ ድረስ መተግበር ስለማትችሉት ነው ወይስ የምር የትጥቅ ትግልን ስለማታምኑበት ነው?

  የትጥቅ ትግልን አናምንበትም። ምክንያቱም የትጥቅ ትግል ሲባል ቀላል ነገር አይደለም፤ የሰው ሕይወትን ይቀጥፋል። የአገር መሠረተ-ልማትን ያወድማል። ከዚህ ባሻገር የጠብመንጃ አስከፊነት የሚያሳዩ ሁለት ተሞክሮዎችን በኢትዮጵያ ማንሳት ይቻላል። አንዱ የወታደራዊው መንግስት ጠብመንጃ ይዞ አገሪቱን 17 ዓመታት ቀጥቅጦ ገዝቷል። በወቅቱ ደርግ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣኑን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ባለመሆኑ በትጥቅ ትግል ሊወርድ ችሏል። ደርግን በኃይል ያስወገደው ኢህአዴግም ደግሞ በተራው ጠብመንጃ በመያዝ የሕዝቡን መብት እንዳሻው እየረገጠ ይገኛል። ሥልጣኑንም ያለ አግባብ ሲጠቀም ቆይቷል።

  ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ነገር በመሳሪያ ኃይል ሥልጣን ላይ የሚመጡ ድርጅቶች ፍፁም ኢ-ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እነሱም ከሥልጣን መውረድ የሚፈልጉት ወደ ሥልጣን በመጡበት አኳኋን ነው። አሁን ነገሮች በጣም እየከረሩ ናቸው። አንዳንድ ገለልተኛ አሁን ያለው ሁኔታ ለተቃዋሚዎች ፈታኝ መሆኑን የሚገልፁ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ በአንፃሩ ደግሞ ተቃዋሚዎች አብረው በመስራት ራሳቸውን የሚያጠናክሩበት መልካም አጋጣሚ ተደርጎም እየተወሰደ ነው

  … የመድረክ ጉዳይ ከምን ደረሰ?

  አሁንም በውይይት ላይ ነን። በቅርብ ጊዜ ውይይቱ ተጠናቆ ውጤቱን ይፋ እናደርጋን።

  ግንባር ነው የሚሆነው ወይስ ውህድ ፓርቲ?

  በአንድነት በኩል ያለው ሐሳብ "ብንዋኻድ ጥሩ ነው” የሚል ነው። ሌሎች ደግሞ ግንባር መሆኑን
  የሚፈልጉ አሉ። ዞሮ ዞሮ በጥንቃቄ እየሰራነው ነው። እያንዳንዱ ድርጅት የየራሱ ተሞክሮ፣ ፕሮግራም እና ርዕዮት-ዓለም ስላለው በችኮላ የሚሆን አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ካሉት የመድረክ አባል ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች ድርጅቶች ፕሮግራማችን የሚመቻቸው ከሆነ መድረኩን እንዲቀላቀሉ በሩን በይፋ ክፍት አድርገነዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመድረክ አባላት ባይሆኑም ከሌሎች ጋር ተባብረን ለመስራት ሁኔታዎችን እያስተካከልን ነው።

  እስኪ አሁን ወደ እርስዎ ልምጣ … "ዶ/ር ነጋሶ ሕብረ- ብሔራዊነት በሚያራምደው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ውስጥ ከገቡ በኋላ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያደርጉትን ትግል ትተዋል” የሚል አስተያየት እየተደመጠ ነው። ምን ምላሽ አለዎት?

  አንድነት ፓርቲ የገባሁበትን ሂደት መለስ ብለን ስናየው … የመድረክ መስራች አባል ነኝ። እና መድረኩ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ሲመዘገብ አንድ ሰው እንደግለሰብ አባል መሆን አይችልም። የግድ የፓርቲ አባል መሆን አለበት። እኔ ደግሞ በወቅቱ የፓርቲ አባለ አልነበርኩ። ስለዚህ የግድ አንዱ ፓርቲ ውስጥ መግባት ነበረብኝና አንድነትን መረጥሁ።

  አንድነትን የመረጥሁበት ምክንያት ፕሮግራሙ በጣም ስለተመቸኝ ነው። ፓርቲው ለግለሰብ መብቶች የሚታገለውን ያህል ለቡድን መብቶች መከበርም እንደሚታገል በፕሮግራሙ ላይ ሰፍሯል። ርዕዩት-ዓለሙ ሊበራል ዴሞክራሲ ቢሆንም ከሶሻሊዝምና ከኮንሰንሰስ ዴሞክራሲ የተቀበለው አለ ይላል። እንደገና ደግሞ የአገሪቱን

  የፖለቲካ ችግሮች በጠብመንጃ ሳይሆን በሰላም መፍታት አለብን። ይሄ ካልሆነ ጉዳዮቹ ላይ ሕዝቡ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ነው የሚለው። ለምሳሌ የፌዴራሊዝምና የሕገመንግስት ጥያቄዎች ላይ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ በሕዝበ-ውሳኔ እንዲፈቱ ነው አቋሙ የሚፈልገው።

  አንድነትም ውስጥ ሆኜ ለኦሮሞ ሕዝብ መብቶች እታገላለሁ። ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የጭቆና ሰለባ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን በመሉ እታገላለሁ። ስለዚህ አንድነት ውስጥ በመግባት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ መከበር እያደረኩት ያለው ትግል በቀጥታ ለኦሮሞም ሆነ ለሌላው ሕዝብ እስከሆነ ድረስ ‹‹ትግሉን ትቷል›› አያሰኝም።_

  ይህ ጽሁፍ ከአውራምባ ታይምስ 4ኛ ዓመት ቁጥር 186 የተወሰደ ነው!

  Views: 571 | Added by: dani | Rating: 4.0/1
  Total comments: 0
  Name *:
  Email *:
  Code *:
  Copyright MyCorp © 2018
  Create a free website with uCoz