Wednesday, 2024-05-08, 4:15 AM
ETHIOPIAN POLITICS current event and news
Main Registration Login
Welcome, Guest · RSS
Site menu
    news
    news
    curency
    Calendar
    «  November 2011  »
    SuMoTuWeThFrSa
      12345
    6789101112
    13141516171819
    20212223242526
    27282930
    Site friends
     
    Main » 2011 » November » 14 » ተንበርካኪው የቤተ-መንግስት ቡድን” እና የስዊድን ጋዜጠኞች በግሩም ታዬ November 14th, 2011
    5:33 PM
    ተንበርካኪው የቤተ-መንግስት ቡድን” እና የስዊድን ጋዜጠኞች በግሩም ታዬ November 14th, 2011

    ህወሀት ለሁለት ከተከፈለ በሁዋላ እነ ስዬ፤ እነ መለስን የሚገልጿቸው፦”ተንበርካኪው የቤተ-መንግስት ቡድን”እያሉ እንደነበር ብዙዎቻችን እናስታውሳለን። ምክንያታቸውም፦”መለስ በምዕራባውያን ተጽዕኖና ትዕዛዝ የሚሽከረከር አሻንጉሊት እንጂ፤ የራሱ የሆነ አቋም የሌለው ልፍስፍስ ሰው ነው” የሚል ነበር። ለዚህም ከማሌሊት ምሥረታ ዋዜማ አንስቶ አስከ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ድረስ ፤አቶ መለስ መልካቸውን ከምሥራቁና ከምዕራቡ ዓለም መስተዋት ጋር ለማስተካከል ያደረጓቸውን በርካታ መገለባበጦች በዝርዝር አስቀምጠዋል።

    በነገራችን ላይ በኢህአዴግ ካምፕ ውስጥ በተለይም በህወሀት አካባቢ፦ "ተንበርካኪ” የሚለው ፍረጃ ከስድብ በላይ የሚጠዘጥዝ እንደሆነ የቀድሞ ታጋዮች ሲያወሩ ይሰማሉ።እነ ተወልደ በህወሀት ክፍፍል ማግስት በየጋዜጣውና በየመፅሔቱ የነ መለስን ወገን፦ "ተንበርካኪው የቤተ-መንግስት ቡድን” ብለው መጥራት የመረጡት፤ቃሉ ግብራቸውን ከመግለጥ ባሻገር እንደ ህመም ይሰማቸው ዘንድ ጭምር በማሰብ ነው ሲሉም እነዚሁ ወገኖች ያክላሉ።(የብአዴን- የትግል ጊዜ መዝሙር ፦ "ያልተንበረከክነው” የሚል መሆኑን ያጤኗል)
    ከዚያ ወዲህ ታዲያ አቶ መለስ "ተንበርካኪ”ነታቸውን ለማስተባበል በሚመስል ሁኔታ ረዥም ርቀት እየሄዱ ምዕራባውያኑን ደጋግመው ሲዘልፏቸውና ሲናገሯቸው ተደምጠዋል፦

    -"እርዳታቸው ይቀራል እንጂ-ቀዩን መስመር እንዲያልፉ አንፈቅድላቸውም!”
    -"በሊማሊሞ ማቋረጥ ይችላሉ!..”
    -"በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ የፈለገ ፈረንጂ ቢንጫጫ፤ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤…
    …..ተከሳሾቹን የሚያስራቸውም፤ የሚፈታቸውም፤ ህጉ እንጂ የፈረንጂ ጩኸትና ተጽዕኖ አይደለም!” ወዘተ… በማለት።

    እነዚህንና ሌሎችን የአቶ መለስን መሰል ንግግሮች፤ ፓርላማ ቀርበው በተናገሩና ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡ ቁጥር መስማት የተለመደ ሆኗል። አቶ መለስ ከዚህም አልፈው በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ የሆኑትን አምባሳደር ዳግላስን ፦ኢዲየት” ሲሉም ተሰምተዋል። አስገራሚው ነገር ታዲያ፤ ይህን ሁሉ ርቀት ሄደው "ጀግና እና ባለ አቋም መሪ” ለመምሰል ያደረጓቸው ሙከራዎች ሁሉ፤" ተንበርካኪ ማንነታቸውን” ሊያስተባብሉላቸው አለመቻላቸው ነው።

    "ለዛሬ አልተሳካልህም፤ ብዙ ይቀርሀል”ነው የሚሉት- የአይድል ዳኞች ቀሽም ዘፋኞች እንደ ቆርቆሮ ሲጮኹባቸው?
    የአቶ መለስም ፦”ሊማሊሞ!ቀይ መስመር፣ ኢዲየት” ወዘተ… ዘለፋዎች፤ ዝም ብለው ከውስጥ የሌሉ ባዶ ጩኸቶች ናቸው-ቆርቆሮዎች።
    በዛ በኩል አርባ ምንጭ ከተማ ላይ ለአሜሪካውያኑ ለአየር ሀይል ቤዝ ማቋቋሚያ የሚሆን ቦታ እየሰጠ፤ በዚህ በኩል፦"የነጭም፣ የጥቁርም ደም እኩል ነው” እያለ በምዕራባውያኑ ላይ የሚፎክርና የሚቆጣ "መሪ” ምን ይሆን የሚባለው? እናቶቻችን የዚህ ዓይነት ሦስት መልክ ያለው ሰው ሲያጋጥማቸው፤-" ስንት እንጀራ ልጋግር-ሰው መስሎ በሸንጎ! ወይም ለማያውቁሽ ታጠኝ!” ይላሉ። ባለፈው ሰሞን ደግሞ አንድ ባለ ሱቅ ጉራጌ ዱቤ አልከፍል ያለውን ደንበኛውን ድንገት አግኝቶት አንገቱን አንቆ እንዲከፍለው ሲጠይቀው፤ ደንበኛው ፀጉሩን እያሻሸ ቢቅለሰለስበት ፦”አውቅሻለሁ፤ የማውቅሽ ቦታ ግን ጠፋኝ አሉ?” በማለት ነበር የተረተበት።
    ብዙዎቻችን ፤ ምናልባትም ሁላችንም እንደምናስታውሰው የምርጫ 97 ግርግርን ተከትሎ ከቅንጅት መሪዎች ጋር በትንሹ ወደ 20 የሚጠጉ ጋዜጠኞች ክስ ተመስርቶባቸው ነበር። ከነዚህ ጋዜጠኞች መካከል አምስቱ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛው ፕሮግራም ክፍል ውስጥ የሚሰሩት ናቸው። ክሱ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ተመስርቶ የችሎቱ ሂደት ተጀምሯል። መንግስት እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈታ በተለያዩ አገሮች ለሚቀርበው ጥያቄ አቶ መለስ፦
    "በህጋችንና በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ አትግቡብን! ቀዩን መስመር እናልፋለን የምትሉ ከሆነ፤ እርዳታችሁን ይዛችሁ ተቀመጡ! የተከሳሾች ጉዳይ የሚያልቀው በህግና በህግ ብቻ ነው!” እያሉ በለመዱት ፉከራ መልስ እየሰጡ ነው።
    የፉከራቸው ጩኸት በጆሮ ላይ ማንቃጨሉን ሳያበቃ፤ የቪኦኤ የቦርድ ሀላፊዎች አዲስ አበባ መጥተው መንግስታቸው በተለይ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ፕሮግራም ክፍል በሚሠሩት ጋዜጠኞች ላይ የመሰረተውን ክስ እንዲያነሳ "ኮስተር” ብለው ተናገሯቸው። አልዋለም፤አላደረም። የቅንጂት እስረኞችን የሚያዬው ችሎት ወዲያው ተሰየመ። ያለምንም ጥያቄና ክርክር ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ተነስቶ፦”በአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞች ላይ የመሰረትኩትን ክስ አንስቻለሁ”አለ።
    "ማርያምን ትወዳታለህ ወይ?”ተብሎ ሲጠየቅ፦ "ወድጄ ነው?! ከድንጋይ የሚያጋጭ ልጂ’ኮ ነው ያላት” ያለው ማን ነበር?
    አዎ! ለአሜሪካ ድምጽ የሚሰሩት ጋዜጠኞች ክስ፤ በብርሀን ፍጥነት ተነሳ፤ ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኞችም – ለሁለት ዓመታት በእስር ይማቅቁ ዘንድ ተፈረደ።
    ነገሩ፤ ኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያዊነቱን ጠልቶ አሜሪካዊነትን ቢመኝ ፤ማነው የሚፈርድበት? የሚያሰኝ ነው።
    አቶ መለስ ግን በማግስቱ ፉከራቸውን ቀጥለዋል፦ " በፈረንጂ ተፅዕኖ የሚታሰርና የሚፈታ ማንም የለም! ተከሳሾች የሚዳኙት በህግና በህግ ብቻ ነው!”እያሉ።

    "ተንበርካኪው የቤተ-መንግስት ቡድን” ከሰሞኑ ደግሞ በበርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና በጋዜጠኞች ላይ ፦”አሸባሪ” የሚል ክስ ለጥፏል። ብዙዎቹን አስሮ፤ጥቂት በማይባሉት ላይ በሌሉበት። ከእስረኞቹ መካከል ሁለቱ ጋዜጠኞች ፤ስዊድናውያን ናቸው-ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን። ለጋዜጠኞች በተከለከለው በሱማሌ ክልል፤ እየሆነ ያለውን ነገር ለመዘገብ ያለ ቪዛ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡት እነዚህ ጋዜጠኞች ፤ ከኦጋዴ ብሄራዊ ነፃነት ግንባር ተዋጊዎች ጋር ሳሉ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መማረካቸው ተሰምቷል።ጋዜጠኞቹ ከተያዙ እለት አንስቶ በእስር ላይ ይገኛሉ።የተመሰረቱባቸውም ክሶች ሁለት ነበሩ- ሽብርተኝነት እና ያለ ቪዛ የአንድን ሉዓላዊ አገር ድንበር ማቋረጥ(መጣስ) የሚሉ።

    በስዊድናውያን ጋዜጠኞቹ ላይ ሁለቱ ክሶች የተመሰረቱት፦ " በኢትዮጵያ ነፃ ፍርድ ቤት አለ” እንዲባል ለታሰበው ድራማ መቼት ይሆን ዘንድ እንጂ፤ "ተንበርካኪው የቤተ-መንግስት ቡድን” ስዊድናውያኑን ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት እንደማይከስ ወትሮውኑም ያወቁ በርካቶች ናቸው። ድርሰቱ ተዓማኒ ይመስል ዘንድ ግን አቶ መለስ ስዊድናውያኑን ጋዜጠኞች አስመልክተውም በአደባባይ መተወንና መፎከር ነበረባቸው። እናም እየጮኹ አሉ፦ " ጋዜጠኞቹ ሽብርተኞች ናቸው።ለዚህ ከበቂ በላይ ማረጋገጫ አለን! እነዚህ ሰዎች ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ውጊያ ላይ ነው የተማረኩት!ይሄ ጋዜጠኝነት ከሆነ አይገባኝም!… በየመን ከአልቃይዳ ጋር ሢሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች በሚሳኤል ሲመቱ፤ አንድም ነገር አልተባለም! እኛ ግን በሚሳኤል አልመታናቸውም! ወደ ህግ ነው ያመጣናቸው!…. የነጭም የጥቁርም ደም ቀይ ነው!…. ”ወዘተ ብዙ አሉ።

    አቶ መለስ በፓርላማ እንዲህ ብለው በፎከሩበት ምሽት ፤ በቀጭን ሽቦ ለፍርድ ቤቱ ያስተላለፉት መልዕክት ከዚህ ተቃራኒ ነው ቢባል ማን ያምናል?-ባታምኑም ያስተላለፉት መልዕክት ይህ ነበር፦ " በነዚህ ፈረንጆች ላይ ሽብርተኛ ብለን የመሰረትነውን ክስ ወደዚያ ጣሉልኝ!”
    የአቶ መለስ የፓርላማ ፉከራና ቀረርቶ ሳምንት ሳይሞላው፦ "በስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተው የሽብርተኝነት ክስ በፍርድ ቤት ውድቅ ሆነ” የሚል ዜና ተሰማ። በዜናው ብዙዎች ተደሰቱ፤ ደስታቸው ግን ብዙ አልቆየም። ከኦብነግ ታጣቂዎች ጋር በተያዙ ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተን የሽብርተኝነት ክስ ውድቅ ያደረገ ፍርድ ቤት፤በነ አብይ ፣ በነ መስፍን ፣በነ እስክንድር፣ በነፋሲልና በነ አበበ ፣በነ ኤልያስ፣በነ ውብሸት፣በነ ስለሽና በነ ርዕዮት ላይ የተለጠፈን የሽብርተኝነት ክስ ተቀብሎ ፦ "ይከላከሉ” የሚል ብይን ሢሰጥ ፤ "እህ ..? እንዴት ነው ነገሩ?” ማለት ጀመሩ።
    የ"ተንበርካኪውን ቡድን” ባህሪ የተረዱ ምስጢር አዋቂዎች ግን፤ አልበረዳቸውም፤አልሞቃቸውም፤አልደነቃቸውምም።
    ይልቁንም፦
    "ሺህ ብትፎክሪ-ሺህ ብትለፈልፊ፣
    ወትሮም አውቅሻለሁ- ካ’ፍ እንደማታልፊ” እያሉ ሲያንጎራጉሩ ነው የሚሰሙት።

    ይህን ያዬና የሰማስ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ኢትዮጵያዊነቱን ጠልቶ ስዊድናዊ ለመሆን ቢመኝ ማነው የሚፈርድበት?!
    ውስጥ አዋቂዎች፤ አቶ መለስ እየደረሰባቸው ካለው የውጪ ተጽዕኖ አኳያ ስዊድናውያኑን አስረው የሚያቆዩበት አቅሙም ሆነ አቋሙም እንደሌላቸው ይናገራሉ።የጋዜጠኞቹን መታሰር ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየመጡባቸው ባሉት ተጽዕኖዎች፤ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውም ታውቋል።የአርቲስት ደበበ እሸቱ ቀድሞ መፈታት ፤ስዊድናውያኑን ለመልቀቅ እንደ መረማመጃ ሳይታይ እንዳልቀረም እነዚሁ የቅርብ ምንጮች ፍንጭ ሰጥተዋል።

    ኢህአዴጎች፦"ግመሎቹ ይሄዳሉ፤ …” እያሉ ራሳቸውን በግመል መስለው ሲመጻደቁብን መኖራቸው ሀቅ ነው። እኛም፦ " ግመል አይደሉም” ብለን አልተቃወምንም።ይሁንና ኢህአዴጎች በተለይም የቤተ-መንግስቱ ቡድን አባላት -ከግመል ጋር የሚመሣሰሉት ወይም የሚቀራረቡት ፤ ከአካሄዳቸው ይልቅ በመንበርከክ ችሎታቸው እንደሆነ ሊያጤኑት ይገባል ነው የምንለው።

    Views: 631 | Added by: dani | Rating: 4.0/1
    Total comments: 0
    Name *:
    Email *:
    Code *:
    Copyright MyCorp © 2024
    Create a free website with uCoz